የኔ ሰው

የኔሰው ሰዎች በቀናነት የሚያደርጉት አስተዋእፆ በምን መልክ ጥቅም ላይ ዋለ የሚለውን ጥያቄ በቀላሉ በሚመልስ መልኩ የተዘጋጀ፣ አንድ ነገር ባደርግ ደስ ይለኛል ለሚሉ ሁሉ ትርጉም ባለው መልክ እርምጃ ለመውሰድ እንዲቀል ሆኖ የተሰራ፣ አዲስ ነገር ሳይሆን በባህላችን ያለውን የመረዳዳት መንፈስ ዘመን የሚያሻግር አገልግሎት ነው።

የቴክኖሎጂ፣ የህክምና፣ የሚድያ እንዲሁም የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን ጨምሮ ከተለያዩ የህብረተስብ ክፍል የተውጣጡ፣ ያገባናል ብለው የተነሱ ዜጎች ህብረት የፈጠረው፣ ለአንድ ግዜ ብቻ ሳይሆን ለዘለቄታው ኢትዮጵያዊ የሆነ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ የመደጋገፍ እንቅስቃሴ በዚህ ዘመን ምን ሊመስል ይችላል ተብሎ ቴክኖሎጂን እንደመሰረታዊ ግባዐት ተጠቅሞ የተቋቋመ እንቅስቃሴ ነው።

የኔሰው አሳታፊ ነው፤ ከዚህ በፌት ወይም ባሁኑ ወቅት ሁሉም ዜጋ ሌሎችን ለማገዝ የሚያደርገውን ጥረት ማድነቅና ማክበር ብሎም ማገዝ አላማው ነው። ከውድድር ትብብር በሚለው መንፈስ የተቃኘ፣ ካለው ለየት ብሎ የተነሳ፣ “እኛ” የሚለው “እኔ” ከሚለው ጠንከር ብሎ የሚገለፅበት መድረክ ነው።

አንዱ መፅዋች ሌላው ተመፅዋች የሚል የማበላለጥ ትርክት ሳይሆን ሁላችንም በአንድ ወቅት ላይ የሌላውን ድጋፍ የምንሻ ማህበራዊ ፍጡሮች ለመሆናችን እውቅና የሚሰጥ አስተሳሰብ ከየኔሰው ጀርባ አለ።

ሰው ያለው ሰው በልበሙሉነት ይራመዳል ነገንም እንዳመጣጡ ይቀበላል። ደስታም ሆነ ሃዘን ሰው ሲኖር ትርጉም ይሰጣል። እኛ ሁላችን አንዳችን ለሌላችን የህይወት ማድመቂያ ነን። የአንዳችን ጉዳት የሁላችንም ነው።

የኔ ሰው የዚህ ሁሉ መረዳት ውጤት ነው። እኛ ለእኛ በቂ ነን።

የኛ ቡድን

ፅዮናዊት ገብረ ዮሃንስ

መልአከፀሐይ መሰለ

ክርስቲያን ተስፋዬ

ሱራፌል አለሙ

ፔጥሮስ ተካ